ከኅዳር 15 ጀምሮ የሚጾመውን ጾመ ነቢያት እንደ እግዚአብሔር ቸርነት ጀምረነዋል:: ለዚኽ ያደረሰን እግዚአብሔር ይመስገን:: የምንራብበት ብቻ ሳይኾን የምንጾምበትና ወደ እርሱም የምንቀርብበት ጾመ ያድርግልን::
ነቢያት የጌታችንን ልደት ለማየት ተስፋውም ተፈጽሞ ድኅነት ተፈጽሞ የሰው ልጅ ወደ ልጅነት ክብሩ እንዲመለሱ ይኽንኑ ለማየት ጾሙ:: በጊዜው ጊዜ ተስፋው ተፈጽሞላቸውም አዩት::
“ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም ታሰናብተዋለህ፤ ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው” በማለትም ፈጣሪያቸውን አመሰገኑት:: ሉቃ 2:29- 32::
ቅዱሳን ነቢያት የአማኑኤልን ልደት ለማየት እንደ ጾሙ እኛ ደግሞ ዳግም ምፅኣቱን በክብር ለማየት እንዲያበቃን በነቢያት እንጻር ሆነን እንጾማለን:: አዎ የጌቶች ጌታ የአምላኮች አምላክ የኾነው ጌታችን በክብር እንዳረገው በክብር በግርማ መለኮት በክበበ ትስብእት ይመጣል:: ለእያንዳንዱ ዋጋውን እንደ ሥራው ይከፍለዋል:: በዚያን ዕለት እንደ በደላችን ሳይኾን እንደ ቸርነቱ እንዲከፍለን አኹን በትሕትና ራሳችንን ዝቅ አድርገን ልንጾም ይገባናል::
የአባቶቻችንና የእናቶቻችን የቅዱሳኑን ጾም ጸሎት የተቀበለ አምላክ የእኛንም ይቀበልልን:: መልካም ጾም::