በምሥጢር የተመላች ታቦት

ድጋሚ የተለጠፈ

በመጋቤ ምሥጢር ስንታየሁ አባተ

በብሉይ ኪዳን እስራኤል ዘሥጋ ለሥርዓተ አምልኮ ከሚገለገሉባቸው ከደብተራ ኦሪትና ከመቅደሰ ኦሪት ንዋያተ ቅድሳተ መካከል አንዱና ዋነኛ የሆነው እጅግም የከበረው የቃል ኪዳኑ ታቦት ነው። ታቦት ማደርያ ማለት ሲሆን ማደርያነቱም ለጽላቱ ነው። ጽላት የሚባለው ደግሞ በእግዚአብሔር ጣቶች ዐሠርቱ ትእዛዛት የተጻፉበት የከበረ ሠሌዳ ነው። “የድንጋይ ጽላቱም በዚህና በዚያ በሁለት ወገን ተጽፎባቸው ነበር። ጽላቱ የእግዚአብሔር ሥራ ነበሩ፤ ጽሕፈቱም በጽላቱ ላይ የተቀረጸባቸው የእግዚአብሔር ጽሕፈት ነበር” እንዲል። ዘጸአ. 32፣15-17።

የቃል ኪዳን ታቦት ተብሎ የሚጠራውም እግዚአብሔር በዚያ ለሕዝቡ ሊገለጥና በዚያም አድሮ ሊባርካቸው ቃል የገባበት ስለ ሆነ ነው።

እግዚአብሔር በጽላቱ ላይ ትእዛዛቱን ጽፎ ለባርያው ለሙሴ ከመስጠቱ በፊት ለጽላቱ ማደርያ የሚሆነውን ታቦት እንዲያዘጋጅ ነገረው። ታቦቱንም በምን ያኽል መጠን፣ ከምን ዓይነት ቁስ ማዘጋጀት እንዳለበት በጥንቃቄ ነግሮታል። በኦሪት ዘጸአት ላይ ተጽፎ እንደምናነበው ታቦቱ ከማይነቅዝ እንጨት እንዲሠራ፣ በንጹሕ ወርቅ በውስጥና በውጪ እንዲለበጥ፣ አራት የወርቅ ቀለበቶች (ቀዳዳዎች) እንዲደረግለት፣ በቀለበቶቹ የሚገቡና ለታቦቱ መሸከሚያ የሚሆኑ መሎጊያዎች ከማይነቅዝ እንጨት ተሠርተው በወርቅ እንዲለበጡ፣ ጽላቱ (ምስክሩ) በታቦቱ ውስጥ እንዲቀመጡ፣ መጠኑ የተገለጠ የሥርየት መክደኛ ከጥሩ ወርቅ እንዲሠራና በታቦቱ ላይ እንዲቀመጥ፣ ከሥርየት መክደኛውም ጋር ሁለት የኪሩብ ምስሎች የሥርየት መክደኛውን በክንፎቻቸው ሸፍነው ፊቶቻቸውን ወደ ሥርየት መክደኛው መልሰው በመተያየት እንዲቆሙ በዝርዝር ተነግሮ እናነባለን። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ በታቦቱ ውስጥ የሚቀመጡትን ንዋያት “ከሁለተኛውም መጋረጃ ወዲያ ቅድስተ ቅዱሳን የምትባለው ድንኳን ነበረች፤ በዚያም ውስጥ የወርቅ ማዕጠንት ነበረ፤ ሁለንተናዋም በወርቅ የተለበጠች የኪዳን ታቦት በእርስዋም ውስጥ መና ያለባት የወርቅ መሶብና የበቀለች የአሮን በትር የኪዳኑም ጽላት ነበሩ” በማለት ዘርዝሯቸዋል። ዕብ 9፣3-4።

ልዑል እግዚአብሔር የታቦቱን ሥራና ከእርሱ ጋር ተያይዘው መሠራት ያለባቸውን ለነቢዩ ለሙሴ በዝርዝር ከነገረው በኋላ የታቦቱን አስፈላጊነትም “በዚያም እገለጥልሃለሁ፤ ለእስራኤል ልጆች የማዝዝኽን ሁሉ በምስክሩ ታቦት ላይ ባለው በሁለት ኪሩቤል መካከል በሥርየት መክደኛው ላይ ሆኜ አነጋግርሃለሁ” በማለት አስረድቶታል። ዘጸአ. 25፣22። 

በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ ለነበሩት ለእስራኤል ዘሥጋ የተሰጠው ይኽ የአምልኮ መፈጸሚያ፣ ከእግዚአብሔር ጋር መገናኛ፣ የእግዚአብሔርም መገለጫ የሆነው ታቦት ከማይነቅዝ እንጨት ተሠርቶ በንጹሕ ወርቅ ተለብጦ በውስጡ ከሚኖሩት ሌሎች ንዋያት ጋር  እንዲገለገሉበት መነገሩ የተሰጣቸው ሥርዓት ምን ያኽል ክቡር እንደ ሆነ ያስረዳል። እንደማይነቅዘው እንጨትና እንደ ንጹሕ ወርቁ  ሕልፈት ውላጤ (መለወጥ) የሌለበት ንጹሐ ባሕርይ የሆነ እግዚአብሔር ወገኖቹ በዙርያቸው ካሉ ከአሕዛብ ጣዖታት ርቀው በንጽሕና ተጠብቀው በምግባር በትሩፋት ተሸልመው እንዲያመልኩት ሊያመለክት የአምልኮ ሥርዓት መፈጸሚያ የሆኑ ንዋያቶቻቸውን ከወርቅና ከማይነቅዝ እንጨት እንዲሠሩ አዘዘ። ይኽ በዚያን ዘመን ለነበሩት ሰዎች እግዚአብሔር የተናገረበት መንገድ ነበር። በዚህ ንባብ ውስጥ ከዚያን ዘመን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ዘመን ለሚነሣው ትውልድስ እግዚአብሔር ምን የተናገረው ነገር ይኖር ይሆን?

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዘመናት ውስጥ እግዚአብሔር ለሕዝቡ በተለያዩ መንገዶች የሚናገር መሆኑን “ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናገረ” ብሏል። ዕብ. 1፣1። እግዚአብሔር ለትውልዱ በምሳሌ፣ ያለ ምሳሌ፣ በሕልም፣ በራእይ ይናገራል። ጻድቁ ኢዮብም “እግዚአብሔር በአንድ መንገድ በሌላም ይናገራል፤ ሰው ግን አያስተውልም” በማለት ይኽን እውነታ አስረድቷል። ኢዮ. 33፣14።

በዚሁ መሠረት ከላይ በዝርዝር ያነሣነው የቃል ኪዳኑ ታቦትና በውስጡ የሚኖሩት ንዋያትም እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን አስቀድሞ በሕሊናው ያሰበውን ነገር በምሳሌ የተናገረበት መንገድ እንደ ሆነ የተለያዩ የነገረ መለኮት ሊቃውንት ያስረዳሉ። የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ይኽን ድንቅ ምሥጢር በዝርዝር አስፍተው አምልተው ተረጉመው አስተምረዋል።

የሥሩግ ኤጲስ ቆጶስ የነበረው ቅዱስ ያዕቆብ ከማይነቅዝ እንጨት ተሠርታ፣ በንጹህ ወርቅ ተለብጣ፣መና ያለባት የወርቅ መሶብ፣ የበቀለች የአሮን በትርና የኪዳኑን ጽላት በያዘችው ታቦት አንጻር በዓለ ትስብእትን አስመልክቶ ባስተማረው ትምህርትእመቤታችንን “በምሥጢር የተመላች ታቦት” ብሎ ገልጧታል። ምክንያቱም ያቺ ታቦት በውስጧ ከያዘቻቸው ንዋያት ጋር በሃይማኖት ልቡና በትሑት ሰብእና ለሚመረምራት እጹብ ድንቅ የሚያሰኙ ምሥጢራትን ይዛ ስለ ተገኘች ነው።

ይኽቺ  ከማይነቅዝ እንጨት ተሠርታ በንጹሕ ወርቅ በውስጥ በአፍኣ ተለብጣ በውስጧ መና ያለባት መሶበ ወርቅ፣ የበቀለች የአሮን በትርና የኪዳኑን ጽላት የያዘችው ታቦት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ መሆኗን ሊቃውንት ያስረዳሉ። ኢትዮጵያዊው የዜማና የመጻሕፍት ትርጓሜ ሊቅ የሆነው ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን ድርሰቱ “ከንጹሐን ይልቅ ንጽሕት የሆንሽ አንቺ ነሽ፤ ከማይነቅዝ እንጨት እንደ ተሠራ በወርቅ እንደ ተጌጠና ዋጋው ብዙ በሆነ በሚያበራ ዕንቊ እንደ ተለበጠ ታቦት በቤተ መቅደስ ውስጥ የኖርሽ የተመረጥሽ ድንግል ነሽ፤ እንዲህ ሆነሽ በቤተ መቅደስ ውስጥ ኖርሽ” በማለት ያቺ በልዩ ሁኔታና ጥንቃቄ የተሠራችው ታቦት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ መሆኗን ተናግሯል። የቃል ኪዳኑ ታቦትና ከእርስዋ ጋር ተያያዥ የሆኑት ንዋያት እንዴት የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ እንደ ሆኑ ከዚህ ቀጥለን እናያለን።

1. የቃል ኪዳኑ ታቦት

እግዚአብሔር ታቦቱን ይሠራ ዘንድ ሙሴን ሲያዘው ስለ እያንዳንዱ ዝርዝር አስረድቶታል። ዘጸአ. 25-30 ተመልከት። ያም በልዩ ሁኔታ የተሠራው ታቦት የእግዚአብሔር ማደርያና የክብሩ መገለጫ ነበር። በዚህ በኦሪቱ የቃል ኪዳን ታቦት እግዚአብሔር ለሕዝቡ በረድኤት ይገለጥላቸው ነበር። እስራኤል ዘሥጋ በምድረ በዳ ታቦቱን ይዘው ሲጓዙ “የእግዚአብሔር ደመና ቀን ቀን በላያቸው ነበረ”። ዘኍል.10፣34። ንጉሥ ሰሎምን ቤተ መቅደሱን በልዩ ክብር ሠርቶ ባስመረቀበት ዕለት ካህናቱም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት በቤቱ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ከኪሩቤል ክንፍ በታች ወደ ነበረው ወደ ስፍራው አመጡት።…….ካህናቱም ከመቅደሱ በመጡ ጊዜ ደመናው የእግዚአብሔርን ቤት ሞላው። የእግዚአብሔርም ክብር የእግዚአብሔርን ቤት ሞልቶ ነበርና ካህናቱ ከደመናው የተነሣ ለማገልገል ይቆሙ ዘንድ አልቻሉም” መጽ. ነገ.ቀዳ. 8፣1-11።

ይኽቺ ታቦት እግዚአብሔር ወልድ በሥጋ ለተገለጠባት ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ናት።ያ በኦሪቱ ለሕዝቡ በታቦቱ ላይ አድሮ ይገለጥ፣ ይራዳ የነበረ እግዚአብሔር በሐዲስቱ አማናዊት ታቦት በቅድስት ድንግል ማርያም በኩል ወደ ሕዝቡ መጣ። በድንግል ማርያም በኩል የመጣው በብሉይ ኪዳን እንደ ነበረው በረድኤት ብቻ ሳይሆን በኵነት፣ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ተዋሕዶ በሥጋ በመገለጥ ነው። “እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና” እንዲል ቅዱስ ሉቃስ።

ቅድስት ድንግል ማርያም የእግዚአብሔር ወልድ ሕያው ማደርያው፣ አዲስና ዘላለማዊት የቃል ኪዳን ታቦቱ ናት። ቅዱስ ሉቃስ የብስራትን ዜና በተናገረበት የወንጌሉ ክፍል በሲና ምድረ በዳ በነበረው የመገናኛ ድንኳንና ንጉሥ ሰሎሞን ባሠራው ቤተ መቅደስ ከተገለጠው የእግዚአብሔር ክብር አንጻር እጅግ በከበረና ከፍ ባለ ሁኔታ በድንግል ማርያም ላይ የሆነውን መገለጥ “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፣ የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፣ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” በማለት አስረድቷል። ሉቃ. 1፣35። በምድረ በዳ ይጓዙ የነበሩትን እስራኤል ዘሥጋን የእግዚአብሔር የክብሩ ደመና እንደ ጋረዳቸው የሐዲስ ኪዳን አማናዊት የቃል ኪዳን ታቦት የሆነችውን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን የልዑል ኃይል ጸለላት።

2. የቃል ኪዳኑ ታቦት ከማይነቅዝ እንጨት ተሠራች

እግዚአብሔር አገልጋዩ ሙሴን ታቦቱን ከማይነቅዝ እንጨት (ከግራር) እንዲሠራው አዘዘው። ግራር ደረቅና ሞቃታማ በሆኑ ቦታዎች በብዛት የሚገኝ እንጨት ነው። እግዚአብሔር ለሕዝቡ በረድኤት መገለጥ ሲሻ የሚገለጥበትን መንገድ ኣሰበ። በቃል ኪዳን ታቦት አድሮ መገለጥም ወደደ። ያንንም ታቦት ከማንኛውም እንጨት እንዲያዘጋጁለት አልፈለገም። እርሱ ባወቀ ከማይነቅዝ እንጨት ብቻ እንዲሆን እንጂ። እንግዲህ በረድኤት ለሚገለጥበት ታቦት ይኽን ያኽል ክብር ያለውን ነገር ካዘጋጀ በአካል ሊገለጥ በወደደ ሰዓት ደግሞ መገለጫው ትሆን ዘንድ የወደዳት ቅድስት ድንግል ማርያምን ምንኛ ንጽሕናን ከቅድስና ጋር አስተባብራ የያዘች አድርጎ እንደ ፈጠራት መገመት አይከብድም። 

ያቺ ምሳሌ የሆነችው ታቦት ከማይነቅዝ እንጨት ተሠርታ በውስጥ በአፍኣ በንጹሕ ወርቅ ከተለበጠች ድኅነተ ዓለምን ይፈጽም ዘንድ የተገለጠባት አማናዊቷ ታቦት ቅድስት ድንግል ማርያም መርገመ ሥጋ መርገመ ነፍስ ያላገኛት፣ በውስጥ በአፍኣ በቅድስና ያጌጠች ናት። በብሉይ ሰውነት ለነበሩ ሰዎች መገለጥ ሲፈቅድ መገለጫውን ከማይነቅዝ እንጨት ሠርተው በንጹሕ ወርቅ ይለብጡ ዘንድ ያዘዘ እግዚአብሔር ዘላለማዊ ቃሉ ለሆነ ልጁ ምንኛ ንጹሕትና ፍጽምት የሆነች ማደርያ ያስፈልገው ይኾን? ለአንድያ ልጁ የአስራ አምስት ዓመት ቆንጆ ማኅፀን ማደርያው ይኾን ዘንድ ከወደደ ምንኛ አንዳች ነውር የሌለባት አድርጎ አዘጋጃቷት ይኾን? ስለ ሆነም ነው ጠቢቡ ሰሎሞን የዚኽችን አማናዊት ታቦት ንጽሕና ተረድቶ “ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው፤ ነውርም የለብሽም” ብሎ የዘመረው። መኃ. መኀ. ዘሰሎ. 4፣7። ቅዱስ ገብርኤልም አማናዊቷ ታቦት የእግዚአብሔር ማደርያነቷ ሊገለጥ በሆነበት ወቅት ሲያበሥራት “ደስ ይበልሽ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፤ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፤ አንቺ ከሴቶች መካከል የተበረክሽ ነሽ” ያላት። ሉቃ. 1፣28። ግራር ከማይነቅዙ እንጨቶች መካከል ተለይቶ ለቃል ኪዳኑ ታቦት መሥርያነት እንደ ተመረጠ ቅድስት ድንግል ማርያምም ከአንስት ዓለም ተመርጣ የእግዚአብሔር መገለጫ፣ ማደርያ ሆነች። 

3. ታቦቱ የጽላቱ፣ የመና ማኖርያ የመሶበ ወርቅና የአሮን በትር ማደርያም ነበር (ዕብ.9፣3-4)

እግዚአብሔር ሊቀ ነቢያት ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በታቦቱም ውስጥ እኔ የምሰጥህን ምስክር ታስቀምጣለህ” ዘጸአ.25፣16። አበው ሊቃውንት እንደ ተረጎሙት ታቦቱ የእመቤታችን ምሳሌ፣ምስክሩ (ጽላቱ) ማኅፀኗን ዓለም አድርጎ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በእርሷ ያደረ የወልድ ዋሕድ ምሳሌ ነው። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ “ከተለዩ የተለየሽ፣ ከከበሩ የከበርሽ ሕግ የተጻፈባት ኪዳን ያለብሽ መና ያለባት መሶበ ወርቅ ያለብሽ ደብተራ ድንኳን አንቺ ነሽ። ይኸውም ሰው ሆኖ በማኅፀንሽ ያደረው የእግዚአብሔር ልጅ ነው” በማለት አብራርቶ አስረድቷል።

በታቦቱ ውስጥ የሚያድረው ጽላትም ከእመቤታችን ጋር ያለውን ተያያዥነት መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው የተረጎሙ ሊቃውንት በስፋት አስረድተዋል። በኦሪት ዘጸአት 34፣1-2 ላይ እግዚአብሔር ሙሴን “ሁለት የድንጋይ ጽላት እንደ ፊተኞቹ አድርገህ ጥረብ፤ በሰበርኻቸው በፊተኞቹ ጽላት የነበሩትን ቃሎች እጽፍባቸዋለሁ” ብሎ እንደ ተናገረው ተጽፏል። ዝቅ ብሎ ከቁጥር 28 ላይም “በጽላቶቹም አሥሩን የቃል ኪዳን ቃሎች ጻፈ” ተብሏል። ኢትዮጵያውያን የብሉይ ኪዳን ሊቃውንት ይኽን ዐረፍተ ነገር “የቀድሞው ጽላት (ሙሴ ተናድዶ የሰበራቸው) የአዳም ምሳሌ፣እምኀበ አልቦ (ካለ መኖር) እንደ ተገኘ አዳምም እንበለ ዘርእ (ያለ ዘር) ለመገኘቱ ምሳሌ፣ ሁለት ወገን መሆኑ የነፍሱ የሥጋው ምሳሌ፣ በጣዖት ምክንያት እንደ ተሰበረ አዳምም በኀጢአት ለመጎዳቱ ምሳሌ፣ የኋለኛው ጽላት የእመቤታችን ምሳሌ፣ እንደ ፊተኛው አድርገህ ቅረፅ  ማለቱ እመቤታችን በዘር በሩካቤ ለመገኘቷ ምሳሌ፣ጽሕፈቱ ጌታችን ከእርሷ የነሣው ሥጋ ምሳሌ፣ ቃሉ የአምላካዊ ቃል ምሳሌ፣ በግብር አምላካዊ መገኘቱ (መጻፉ) ጌታም ያለ ወንድ ዘር ለመወለዱ ምሳሌ” በማለት ተርጉመውታል።

በታቦቱ ውስጥ ከድንጋይ በተቀረፀ ጽላት ላይ የተጻፉ ዐሠርቱ ትእዛዛት (የእግዚአብሔር ቃል) ነበሩ። ከድንግል ማርያምም አካላዊው ቃል ባሕርይዋን ነስቶ ተዋሕዶ በማኅፀንዋ አደረ። በታቦቱ ውስጥ እስራኤል ዘሥጋ በምድረ በዳ ሳሉ ይመገቡት የነበረውና ከሰማይ ይዘንምላቸው የነበረው መና ነበር። በአማናዊቷ ታቦት በድንግል ማርያም ማኅፀን ከሰማይ የወረደውና ዘላለማዊ ሕይወትን የሚሰጠው የሕይወት እንጀራ ነበር። እርሱም ልጅዋ ወዳጅዋ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ዮሐ. 6፣ 35-51። በታቦቱ ውስጥ የክህነቱ ማረጋገጫ የሚሆን ሳትተከል ውኃ ሳትጠጣ ለምልማ አብባ አፍርታ የተገኘች የአሮን በትር ነበረች። በታቦት የተመሰለችው ድንግል ማርያምም አስራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ ኖራ ያለ ወንድ ዘር ያለ ሰስሎተ ድንግልና በውስጥ በአፍኣ በንጽሕና በቅድስናና በድንግልና ተጠብቃ እውነተኛ ካህንና ሊቀ ካህናት የሆነውን ጌታ ጸንሳ ተገኘች።

4. የእግዚአብሔር ታቦትና ንጉሥ ዳዊት

ከእስራኤል ሕገ እግዚአብሔርን መተላለፍ የተነሣ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት በፍልስጥኤማውያን ተማርካ ተወሰደች።ንጉሥ ዳዊት ከነገሠ በኋላ ከእርሱ ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ በይሁዳ ካለች ከበኣል ተነሥተው በኪሩቤል ላይ በተቀመጠ በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም የተሠራውን የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጡ ዘንድ ሄዱ። 2ሳሙ. 6፣1-5። የእግዚአብሔርን ታቦት በአዲስ ሰረገላ አድርገው ወደ አቢዳራ ቤት እየወሰዱት ሳለ የእግዚአብሔር ቁጣ ለታቦቱ ተገቢውን ክብር ባልሰጡ በአሚናዳብ ልጆች ላይ በተለይም በዖዛ ላይ ነደደ። ዖዛ ያለ ሥልጣኑ የቃል ኪዳኑን ታቦት በመያዙ ተቀሠፈ። ይኽን ድንቅ ተአምራት ያየ ዳዊት “እግዚአብሔርን ፈራና የእግዚአብሔር ታቦት ወደ እኔ እንዴት ይመጣል?” አለ። 2ሳሙ. 6፣9።

አማናዊት ታቦት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከመልአኩ እንደ ተነገራት ቃል እርሷም “እንደ ቃልህ ይኹንልኝ” ብላ ከተቀበለች በኋላ ጌታን ጸንሳ ሳለ ዘመዷ የምትሆን ቅድስት ኤልሳቤጥን ልትጠይቃት ወደ ተራራማው አገር ወደ ይሁዳ ከተማ ፈጥና ወጣች። ወደ ዘካርያስም ቤት ገብታ ኤልሳቤጥን በተሳለመቻት ሰዓት ያቺ ቅድስት ኤልሳቤጥ እመቤታችንን “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይኾንልኛል?” ብላ አድንቃ ተናገረች። ሉቃ. 1፣43።  ቅዱስ ዳዊትም ቅድስት ኤልሳቤጥም ተመሳሳይ ቃል በተለያዩ ዘመናት በይሁዳ ምድር ተናገሩ። የእግዚአብሔር ማደርያ የሆነችውን የቃል ኪዳን ታቦት ክብር ባየ ጊዜ ቅዱስ ዳዊት እንዳደነቀ ቅድስት ኤልሳቤጥም የእግዚአብሔር ወልድ ማደርያ የሆነችው ድንግል ማርያም ትጠይቃት ዘንድ ወደ ቤቷ በገባችበት ወቅት ተደነቀች።

5. የቃል ኪዳኑ ታቦት በአቢዳራ ቤት

የቃል ኪዳኑ ታቦት ከፍልስጥኤማውያን ዘንድ ሲመለስ የጌት ሰው በሚሆን በአቢዳራ ቤት ሦስት ወር ያኽል ተቀመጠ። እግዚአብሔርም አቢዳራንና ቤቱን ሁሉ ባረከው። 2ሳሙ. 6፣11።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምም ከመልአኩ ብሥራትን ተቀብላ ጌታን ጸንሳ ሳለ ወደ ካህኑ ወደ ዘካርያስ ቤት ልትጠይቃቸው ሄደች። “ማርያምም ሦስት ወር የሚያኽል በእርስዋ ዘንድ (በኤልሳቤጥ ዘንድ) ተቀመጠች። ወደ ቤትዋም ተመለሰች።ሉቃ.1፣56። አቢዳራና ቤተሰቦቹ  ምሳሌ የምትሆነውን የብሉይ ኪዳን ታቦት ለማስተናገድ በመብቃታቸው ከተባረኩ አማናዊት የሐዲስ ኪዳን ታቦት እውነተኛውን ጽላት በማኅፀኗ የያዘችውን በቤታቸው የተቀበሉ ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ምንኛ ተባርከው ይኾን?

6. ንጉሥ ዳዊት በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት

ንጉሥ ዳዊት የቃል ኪዳኑ ታቦት በዖዛ ላይ ያደረገውን ተአምር ባየ ጊዜ ወደ ቤቱ ለመውሰድ ፈርቶ ነበር። ነገር ግን የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ አቢዳራ ቤት ገብቶ ቤቱን ሁሉ እንደ ባረከለት ሲሰማ ወደ ከተማው ሊያመጣው ወደደ። አስመጣውም። ያ በአእላፈ እስራኤል ዘንድ የተከበረ፣ የታፈረና የተወደደ ንጉሥ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ልብሰ ንግሥናው ከራሱ ላይ ወርዶ እስኪራቆት ድረስ በሙሉ ኀይሉ እየዘለለ ፈጣሪውን አመሰገነ። 2ሳሙ. 6፣12-19።

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ዘካርያስ ቤት ገብታ ቅድስት ኤልሳቤጥን ሰላም ባለችበት ወቅት በኤልሳቤጥ ማኅፀን ውስጥ የነበረው ቅዱስ ዮሐንስ በደስታ እየዘለለ የፈጣሪውን እናት፣ የፈጣሪውን ማደርያ ተቀበለ። “ኤልሳቤጥም የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ ፅንሱ በማኅፀንዋ ውስጥ ዘለለ” እንዲል። ንጉሡ በቃል ኪዳን ታቦቱ ፊት እየዘለለ የዘመረው የታቦቱ ክብር ምንኛ ቢገባው ይኾን? የስድስት ወር ፅንስ ቅዱስ ዮሐንስስ ገና በማኅፀን ሳለ በአማናዊቷ ታቦት ፊት የሰገደው ምንኛ የድንግል ክብር ቢገባው ይኾን?

በቃል ኪዳኑ ታቦትና በአማናዊቷ ታቦት በድንግል ማርያም መካከል ያለውን መመሳሰል ዘርዝረን አንዘልቀውም። ነገር ግን ከቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊው ጋር “በክብር ከፍ ከፍ ያልሽ ደንግል ሆይ በእውነት አንቺ ከከበሩት ሁሉ ይልቅ ትከብርያለሽ።የእግዚአብሔር ቃል ማደርያ ድንግል ሆይ በክብር ማን ይተካከልሻል? ከፍጡራን ሁሉ ከማን ጋር ላወዳድርሽ? ድንግል ሆይ አንቺ ከሁሉም ትልቂያለሽ። በኀላፊ በጠፊው ወርቅ ያይደለ በንጽሕና ጌጥ ሁሉ ያጌጥሽ አማናዊቷ የቃል ኪዳን ታቦት ሆይ አንቺ እውነተኛ የሆነ መና ያለብሽ የወርቅ መሶብ ነሽ፤ ያውም አካላዊው ቃል ማደርያው ያደረገው ንጹሕ ሥጋሽ ነው።”

ቅዱስ ያዕቆብ ዘሥሩግ በእውነት እመቤታችንን “በምሥጢር የተመላች ታቦት” ብሎ መጥራት ተገባው። እርሷ ከዚያች በብሉይ ኪዳን ከተገለጠችው እስራኤልም ይመኩባት ከነበረችው ታቦት ትበልጣለች። ያቺ ታቦት የተመኩባትን፣ በፊትዋ ዕለት ዕለት የሚያገለግሉትን ለገነት፣ ለልጅነት አላበቃችም። እኛ ግን በአማናዊቷ ታቦት በቅድስት ድንግል ማርያም የማኅፀንዋ ፍሬ ለልጅነት ለገነት ለመንግሥተ ሰማያት በቃን። ያቺ የተማጸኑባትን ከምድራዊው መከራ ብቻ ታደገች። እመቤታችን ቅድስት  ድንግል ማርያም ግን ከልጅዋ ከወዳጅዋ በተሰጣት የአማላጅነት ቃል ኪዳን የተማጸኗትን ሁሉ ከሰማያዊ መከራ ከመከራ ሥጋ ከመከራ ነፍስ ሁሉ ትታደጋለች።

ስለዚህ እንደ አቢዳራ በፍቅር ወደ ቤት ልቡናችን ከነ ሙሉ ክብሯ እንቀበላት። እንደ ቅዱስ ዳዊት በፊቷ እየዘለለልን “የእግዚአብሔር ከተማ ሆይ በአንቺ የተከበረ ነገር ይባላል” እያልን እንዘምር። መዝ. 86፣3። እግዚአብሔር አምላካችን የእመቤታችንን ፍቅሯን በልቡናችን ጣዕሟን በአንደበታችን ያሳድርብን። አሜን።      

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: