መጠጊያ ያጣው አምላክ

እግዚአብሔር የዓለሙ ኹሉ መጠጊያ ነው። ሕይወት የተገኘው ከእርሱ ነው። ሕይወት ሕይወት ኾኖ የሕይወትንም ትርጉምና ተግባር ይዞ የሚገኘው በመድኃኔዓለም ቸርነት ነው። ቅዳሴያችን “አንተ ውእቱ ምርኩዘ ጻድቃን፣ ተስፋሆሙ ለስዱዳን፣ መርሶሆሙ ለእለ ይትሀወኩ፣ ብርሃነ ፍጹማን” እንዳለው እርሱ ጻድቃንን በገድላቸው ኹሉ የሚያበረታ ምርኩዝ፣ ከሀገር ከወገን በተለያዩ ምክንያቶች ተገፍተው ወጥተው ለተሰደዱት ተስፋና መጠጊያ፣ በዚኽ ዓለም የመከራ ማዕበል ለሚታወኩት የጸጥታ ወደባቸው ፍጹማንን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያገባቸው የጽድቅ ብርሃን ነው።

የሰው ልጅ በዚኽ ዓለም የሚጠጋበት ቤት አለው። በገንዘቡ በሠራው፣ በተከራየው፣ በውርስ ወይም በስጦታ ባገኘው ቤት ይኖራል። እግዚአብሔርም የሰውን ልጅ በራሱ አርአያና ምሳሌ ሲፈጥረው ዓላማው ሰው የእርሱ ማደርያ የክብሩ መገለጫ እንዲኾን ነበር። ስለኾነም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደኾናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንዲያድርባችሁ አታውቁምን?” እንዳለው ሰው የእግዚአብሔር ማደርያ ነው። 1ቆሮ. 3፥16። በስሙ አምነን ስንጠመቅ ቅዱስ ሥጋውን ስንበላ ክቡር ደሙን ስንጠጣ በበጎ ምግባር ሕይወታችንን ስንመራ የእርሱ ማድርያ እንኾናለን።

አንድ ሰው መኖርያ ይኾነኛል ብሎ የሠራው ቤት የአራዊት፣ የተባይ፣ የሌቦችና የቀማኞች ማድርያ ከኾነ ሊያድርበት አይችልም። በተቻለው መጠን ሊያጸዳው ይሞክራል። ካልኾነም ወይ ይሸጠዋል አለያም ያፈርሰዋል። እግዚአብሔርም በማድርያዎቹ ውስጥ ከክብሩ ጋር የማይሄድ ባዕድ ነገር ሲያይ ሊኖርበት አይችልም። አስቀድም ያ የእርሱ ማደርያ የኾነው ግለሰብ የእግዚአብሔር ማድርያነቱን ሊያቆሽሹት ከሚችሉ ነገሮች እንዲጠበቅ ይመክረዋል፤ ይግሥፀዋል። በዚህ ኹሉ አልመለስ ካለ ለማይረባ አእምሮ አሳልፎ ይሰጠዋል።

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሚያስተምርበት ወቅት በርካታ ሰዎች ለተለያዩ ፍላጎቶቻቸው ይከተሉት ነበር። እርሱም እንደየእምነታቸውና እንደየልቡናቸው ቅንነት መሻታቸውን ይፈጽምላቸው ነበር። ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጎበዝ ወደ እርሱ ቀርቦ እንዲህ አለው። “ወደምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ።” ማቴ.8፥19። በእውነቱ ከኾነ የዚኽ ወጣት ጥያቄ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ነው ከላይ ሲያዩት። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የኾነው ከእርሱ ርቀው የዓለሙና የዲያብሎስ ተከታይ የኾኑትን ከዘላለም ሞት ታድጎ የእርሱ ደቀ መዛሙርት ወይም ተከታዮች ሊያደርጋቸው ነው። ይኹን እንጂ ከወንጌሉ እንደምናነበው ጌታ የዚኽን ሰው የልከተልህ ጥያቄ አልተቀበለውም። ቅዱስ ማቴዎስ ጉዳዩን “ኢየሱስም ለቀበሮዎች ጉድጓድ ለሰማይ ወፎችም መሳፈርያ አላቸው። ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው” በማለት ጽፎልናል። ማቴ. 8፥20።

ይኽን ታሪክ ባነበብኩ ቁጥር ይገርመኛል። እንዴት ሊሆን ቻለ? ምክንያቱም በዚሁ ምዕራፍ ላይ በቀጣዩ ቁጥር ላይ ደግሞ ሌላኛው ጎበዝ “ጌታ ሆይ አስቀድሜ አንድሄድ አባቴን እንድቀብር ፈቀድልኝ” ብሎ እንደለመነውና ጌታም “ተከተለኝ፣ ሙታን መታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው” እንዳለው ተጽፏል። ማቴ. 8፥21- 22። ለዚህ ቃል አንክሮ ይገባል። በውኑ እግዚአብሔር ያዳላልን? በፍጹም!!!! ስለምን ያኛውን እምቢ ብሎ ይኼኛውን እሺ አለው?

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት “እግዚአብሔር ልቡናንና ኩላሊትን ይመረምራል” ይላል። መዝ. 7፥9። ቅዱስ ጳውሎስም ማንነታችንና ሥራችን በፊቱ የተገለጠ መኾኑን “እኛን በሚቆጣጠረን በእርሱ ዓይኖቹ ፊት ሁሉ ነገር የተራቆተና የተገለጠ ነው እንጂ በእርሱ ፊት የተሰወረ ፍጥረት የለም” ብሏል። ዕብ. 4፥13። እርሱ ገና በማኅጸን ሳለን ያውቀናል። ከጊዜ ውጪ የኾነው አምላካችን በጊዜ የምንገደብ እኛን ሳይፈጥረን በሚሰጠን ነጻ ፈቃድ ምን እንድምንኾን ምን እንደምንሠራበት ያውቃል።

ከላይ ጌታችንን “ልከተልህ ያለው ጎበዝ ከጸሕፍት ወገን የኾነ ሰው። ጸሐፍት ደግሞ ራሳቸውን አዋቂዎችና ከሌሎች የተሻሉ አድርገው የሚያስቡ ናቸው። ይኽ ጎበዝ ይኽ የወገኖቹ የትዕቢት መንፈስ የተጠናወተው ሰው ነበር። ትዕቢት የሰይጣን ገንዘብ ነው። ሊቀ መላእክት የነበረውን ሳጥናኤልን ከማዕረጉ ያዋረደው ከሹመት የሻረው ይኽ ትዕቢቱ ነበር። ትዕቢተኛ ሰው የሰይጣን ማደርያ ነው። የዲያብሎስ ማደርያ በኾነው ደግሞ እግዚአብሔር ሊያድርበት አይችልም። ምክንያቱም “ክርስቶስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? … ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ከጣዖት ጋር ምን መጋጠም አለው?” ተብሏልና ነው። 2ቆሮ. 6፥14 – 17።

በርካታ ዓመታት ወይም ወራት በጸሎታችን እግዚአብሔር ማደርያው እንዲያደርገን ጸልየን ይኾናል። እግዚአብሔር በክብር የተገለጠባቸውን ቅዱሳንና ቅዱሳት ገድል ስናነብ ወይም ስንሰማ እንደነርሱ እኛንም ማደርያዎቹ እንዲያደርገን ተማጽነን ይኾናል። ይኽ መንፈሳዊ መሻታችን አልሟላልን ብሎን በልቡና ስብራት “ጌታ ሆይ መች ነው የምትጎበኘኝ?” ብለን ሙግት እስከመግጠም የደረስንም እንኖራለን። ኀጥአን መጸብሐንን የጎበኘ ማድርያውም ያደረገ አምላክ ለእኛ ለምን ዘገየ? መጎብኘቱን እንዲያዘገይ ያደረገው አንዳች ችግር እኛ ዘንድ ይኖር ይኾን? ጠቢቡ “በተራሮች ላይ ሲዘልል በኮረብቶችም ላይ ሲወረወር ይመጣል” ያለለት አምላካችን በእውነቱ ለምን ዘገየብን? መኃ. መሐ. 2፥8።

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕለት ዕለት ወደ ሕይወታችን ይመጣል። በበረከቱ ሊባርከን፣ ከሸክማችን ኹሉ ሊያሳርፈን፣ ከጭንቀታችንና ከኀዘናችን ሊያጽናናንና ሊያረጋጋን፣ ጉድለታችንን ሊሞላ ልባችንን ሊያሳርፍልን ወደ እኛ ይመጣል። ይኽንንም ለቅዱስ ዮሐንስ ባሳየው ራእይ “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፣ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ፣ ከእርሱም ጋር ራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል” ብሏል። ራእይ 3፥20። እንዲህ ያለ ጌታ ስለምን ዘገየብን?

እግዚአብሔር ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም። ቅዱስ ጴጥሮስ “ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም” እንዳለው። ነገር ግን እንደዚያ ጎበዝ ጸሐፊ በውስጣችን የሚያያቸው ክፋትና ተንኮል፣ ትዕቢትና ምቀኝነት ያዘገዩታል። በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ወገን ለነበሩት ለእሥራኤል ዘሥጋ በነቢዩ በኩል የተነገራቸው ቃል ይኽን እውነታ ያስረዳል። “እነሆ የእግዚአብሔር እጅ ከማዳን አላጠረችም፤ ጆሮውም ከመስማት አልደነቆረችም፤ ነገር ግን በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ልይታለች፤ እንዳይሰማም ኃጢአታችሁ ፊቱን ከእናንተ ሰውሮታል” እንዲል። ኢሳ.59፥1-2። ይኼ እውነታ ነው “በሄድክበት ልከተልህ” እያለ የለመነውን ጸሐፊ “የሰው ልጅ ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” የሚል ቃል ከጌታችን አንደበት አንዲሰማ ያደረገው።

እግዚአብሔር ያላደረበት ሕይወት ደግሞ መጨረሻው አይምርም። ይሁዳ ጌታን ከልቡናው አስወጥቶ ፍቅረ ንዋይን በልቡናው አዳራሽ ሾመበት። ፍጻሜው ግን ገንዘቡንም የዘላለም ቤቱ የኾነውን መድኃኔዓለምንም ማጣት ኾነ። ስለዚህ የሚበጀን ፈጥኖ ንስሐ መግባት ብቻ ነው። የሚበጀን ከመንገድ ዳር ተቀምጦ እንግዳ ይቀበል እንደነበረው አብርሃም “አቤቱ ባርያህን አትለፈኝ” ብሎ መማጸን ነው። የሚበጀው እንደ ቃና ዘገሊላ ጋኖች ከሰው ሠራሽ የወይን ዝቃጭ ባዶ ኾኖ (በንስሐ) ራስን ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠት ነው። የሚጠቅመው ከአምላካችን ፍቅርና መጎብኘት የራቀውን ሕይወታችንን “ልጄ ሆይ የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” ብላ እንደማለደች እንድትማልድልን እመቤታችንን ዘወትር በእምነት ጸሎት አማልጂን ብሎ መማጻን ብቻ ነው። ያን ጊዜ ራሳችንን በሀብት፣ በዝና፣ በዕውቀት፣ በዘመድ፣ በሥልጣን፣ በመልክ፣ በጉልበት ከመመካት ባዶ አድርገን ዝቅ ስናደርግ እርሱ ደግሞ በረድኤት ያድርብንና ጉድለታችንን ኹሉ ይሞላዋል። ለርስቱም ያበቃናል። የመድኃኔዓለም ቸርነት፣ የእመቤታችን አማላጅነት አይለየን።

እግዚአብሔር ዘወትር ወደ በጎ ፈቃዱ ይጠራናል። ለክብር ይጠራናል። ግን ጥሪውን ተከትለን ለክብር እንዳንበቃ የሚያደርጉንና እግዚአብሔር በውስጣችን የሚመለከታቸውን ክፋትና የሥጋ ፈቃዳትን በንስሐ ልናስወግድ ይገባናል። የዘረኝነት፣ የትዕቢት፣ የስካር፣ የዝሙት፣ የመለያየት፣ የመፍረድ፣ የመወነጃጀል፣ የመጠላለፍ፣ የማማረር፣ የክፋት ኹሉ ማድርያ ስንኾን በሚያሳዝን ቃሉ “ለቀበሮ ጉድጓድ ለሰማይ ወፎች መሳፈርያ አላቸው። ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” ይለናል። ዓለም የሌላ ማደርያ ኾናለች። ሰማይ ዙፋኑና ማደርያው የኾነ አምላክ ድል በነሡና በሰማያውያን ቅዱሳን የሚያድር እግዚአብሔር በምድር ግን ራሱን መጠጊያ እንዳጣ አድርጎ “ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” ይለናል። በቤተ ልሄም መጠጊያ አጥቶ በከብቶች ግርግም የተወለደው ጌታ በዘመናችን በክርስቲያኖች ልቡና፣ በቤተ ክርስቲያኑ መጠጊያ አጥቷል። እጅግ ውድ በኾኑ ኣዕባን የተሠሩ አብያተ ክርስቲያናት ቢኖሩም በስንታቸው ውስጥ ይኾን እግዚአብሔር የሚገኝባቸው? “ለዘላለም ስሜ በዚያ ያድር ዘንድ ይኽን የሠራኸውን ቤት ቀድሻለሁ፤ ዓይኖቼናቅ ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይኾናሉ” ያለ አምላክ በዘመናችንስ ዓይኖቹና ልቡናው በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ይኾን? ቤቱ የምስጋና የአምልኮ የትምህርት የንስሐ የቅድስና የትሕትና መኾኑ ቀርቶ የሙስና፣ የዘረኝነት፣ የክፋት ኹሉ መሰብሰቢያ መኾን ከጀመረ ሰነበተ። ታድያ እንዴት በዚያ አድሮ ልመናችንን ይስማን?

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: