ኑኀሚንና ቤተሰቦቿ

ኑኀሚንና ቤተ ሰቦቿ በሞዓብ ምድር የሚበሉትን ምግብ አግኝተው ልጆቿ በባዕድ ምድር ከሞዓባውያን ሴቶች አግብተው ትዳር መሥርተው መኖር ጀምረው ነበር። ከአንደኛው መከራ ለማምለጥ አንድ እግራችንን ስናነሣ ሌላኛውን መከራ ከፊታችን እናያለን። ኑኀሚን ባልጠረጠረችው ሰዓት ባለቤቷም ሁለት ልጆቿም ሞቱ። አራት ሁና ወጥታ ብቻዋን ቀረች። ልጆቿ ትዳር ቢይዙም ዘር አልተኩላትም ነበር። ግን ለምን?

ሕይወት አንድ መልክ የላትም። ሰው መሆንም አንዱን የሕይወት ገጽታ ብቻ ማየት አይደለም። ሁሉን እንደየሁኔታው ማየት ካልቻልን የመልካሙን መልካምነት፣ የክፉውን ክፋት፣ የእምነታችንን ጽናት፣ የእግዚአብሔርን ቸርነት እንዴት እናውቃለን? ኑኃሚን የመምለኬ እግዚአብሔር የአብርሃም ልጅ ናት። ግን ተራበች፤ተሰደደች፤ ልቡናን የሚሰብር ኀዘን በስደት ሀገር አገኛት።

በተመሳሳይ መልኩ የተሻለ ፍለጋ ከቀዬያቸው ወጥተው ከሀገራቸው ርቀው በሄዱበት ስፍራ መከራ የሚቀበሉ በአሕዛብ ተይዘው ወይ እምነታችሁን ቀይሩ አለያም በሰይፍ እንገድላችኋለን ተብለው የተገደሉ፣ ጀልባቸው ተሰብሮባቸው የዓሣ እራት የኾኑ ክርስቶሳውያን ምእመናን ብዙ ናቸው። የመከራው ዓይነት፣ የአስጨናቂዎቻቸው ብዛት፣ የችግሩ ጊዜ መርዘም በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት የተፈታተነባቸው በቀላል ቁጥር አይገመቱም። ያዋጣናል ብለው በገቡበት ስደት፣ ትዳር፣ ሥራ፣ አገልግሎት ያልጠበቁት ነገር ሲያጋጥማቸው የልቡናቸው መታጠቂያ መቀነት የሚላላባቸው አሉ።

የዚኽን ምሥጢር ኦሪትም ወንጌልም አስቀድመው ገልጠዋል። ኦሪተ ሙሴ “ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች” ትላለች። ዘፍ.3፣17-18። በዚህ ቃል መሠረት የምንኖርባት ምድር በብዙ ድካም የምንንገላታባት፣ በእሾህና በአሜከላ (በፍትወታት ወ እኩያት) ተመልታለች። ምድር ሰውነታችንም ስንፈጠር የሌለብንን ክፋትና ተንኮል እያበቀለችብን ኑሮአችንን ታመርርብናለች። እዚህ ላይ ምናልባት ያ በአዳም መተላለፍ ያገኘን መርገም በክርስቶስ ቀርቶልን የለምን? የሚል ጠያቂ ሊኖር ይችላል። በርግጥ በአዳም የሄደችውን ልጅነት በክርስቶስ የማዳን ሥራ (ኢኮኖሚ ኦፍ ሳሊቬሽን) አግኝተናል። መርገማችን በመስቀል ላይ በፈሰሰው ደሙ ተቀድሷል። ይኹን እንጂ የሥጋ ሞት እስከ ትንሣኤ ዘጉባኤ ድረስ እንዳልቀረልን ሁሉ በዚህ ዓለም መቸገርም አለ።

ወንጌለ ክርስቶስም በጌታችን በአምላካችንና በመድኃለታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት ያመኑ፣ በኑሮአቸው ሁሉ ይመስሉትም ዘንድ በስሙ የተጠመቁ የተጠበቀላቸው መከራና ፈተና እንዳለ ትናገራለች። “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ” እንዲል። ዮሐ.16፣33። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ስለ እርሱ መከራ ደግሞ ልትቀበሉ እንጂ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አይደለም” ብሏል። ፊል.1፣29።

የአብርሃም ልጅ ኑኀሚን ከቅድስት ሀገር ወጥታ በሞዓብ ምድር ድርብ መከራ እንዳገኛት ሁሉ የክርስቶስ ልጆች ምእመናንም ከቅድስት ርስታቸው ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አፍኣ በሆነችው በዚህች ዓለም በርካታ መከራዎች ይቀበላሉ። ዋናው ነገር መከራ መቀበላቸው ሳይሆን የመከራው መንሥኤ ከየት ነው? የሚለው ነው። መከራ ከራስ ኀጢአት፣ ከሰይጣንና እምነታችንና ክብራችን ሊገለጥበት በእግዚአብሔር ፈቃድ እንደ ኢዮብ የምንፈተንበት ጊዜ ይኖራል። ከራስ ኀጢአት የሚመጣውን መከራ በንስሐ፣ ሌላውን በጾም በጸሎት፣ በምስጋና ልናሳልፈው ይገባናል።

ረሃብ የሥጋ ብቻ አይደለም፤ የነፍስም ጭምር እንጂ። የነፍስ ረሃብ ከቃለ እግዚአብሔር እጥረት፣ በመናፍቃን የማሳት ወጥመድ ከተበረዘ “ቃለ እግዚአብሔር”፣ በእምነት ከመዛል፣ ከመጥፎ ውሎ፣ ከተከታታይ ፈተና፣ ተስፋ ከመቁረጥ፣ ከንስሐ በመራቅ፣ ከሥጋ ወደሙ ከመለየት፣ ኀጢአትን እንደ ዋዛ ከመለማመድ የተነሣ ይከሰታል። ረሃብ ታላቋን እናት ኑኃሚንን ከቤተ ልሔም ወደ ሞዓብ ምድር እንድትሰደድ አደረጋት። የነፍስ ረሃብ ታላቁን ሰው በክርስቶስ የማዳን ሥራ ለሰማያዊ ክብር የታደለውን ምእመን ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት ይለያል። ለስደት ማለት ለጉስቁልና ኑሮ ይዳርጋል። አዳም እንደ ተራቆተ ከጸጋ እግዚአብሔር ያራቁታል። እንደ ጠፋው ልጅ ከሰው ለይቶ ከእርያ (ከአጋንንት) ጋር ያውላል። ኑኃሚን በረሃብ ተሰድዳ በሄደችበት አገር ባለቤትዋንና ልጆችዋን አጣች። በነፍስ ረሃብ ከሀገራችን ከጽድቅ ሕይወት፣ የሰማይ ደጅ ከተባለችውም ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና ሥርዓት ስንለይ ባል በሚስቱ ላይ እንደሚሠለጥን በእኛ ላይ የሰለጠነውን መድኃኔዓለምን እናጣዋለን፤ ልጆችዋን እንዳጣችው ከምግባር ከትሩፋት ባዶ እንሆናለን። ኑኀሚን በአሕዛብ ምድር ብቻዋን እንደ ቀረችው በነፍስ ረሃብ ስንያዝ በዚህች ዓለም ብቸኞችና ተቅበዝባዦች እንሆናለን። እንግዲህ ለዚህ ነው ጠቢቡ ሰሎሞን “የጠገበች ነፍስ የማር ወለላ ትርግጣለች፤ ለተራበች ነፍስ ግን የመረረ ነገር ሁሉ ይጣፍጣታል” ያለው። ምሳሌ 27፣7። ነፍስ በቃለ እግዚአብሔር፣ በንስሐ፣ በሥጋ ወደሙ፣ በፍቅር፣ በትሕትና፣ በሰላም፣ በመንፈስ ፈቃዳት ሁሉ ስትመላ ጣፋጭ መስሎ የሚያታልለውን የዚህን ዓለም ክብር ትንቃለች። ከተራበች ግን ነውሩ ክብር፣ ውርደቱ ልዕልና፣ ኀጢአቱ ጽድቅ፣ ክህደቱ እምነት መስሎ ይታያታል። እስቲ ወደ ልቡናዎት ይመለሱ። ነፍስዎት ጠግባለች ወይስ ተርባለች?

የኑኃሚን አራት ሁና ወጥታ ብቻዋን መመለስ  (ይቀጥላል)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: