ኑኀሚንና ቤተሰቦቿ

ክፍል ሁለት

                  

በክፍል አንድ ኑኀሚን ከሀገሯ በረሃብ ምክንያት መውጣቷንና ያንን ተከትሎ የደረሰባትን ከባድ ኀዘን ተመልክተን ከራሳችን ሕይወት ጋር ለማስተያየት ሞክረናል። ሁለተኛውን ክፍል ቀጥለን አብረን በጋራ እናያለን። እግዚአብሔር ማስተዋሉን ይስጠን።

ኑኀሚን አራት ሁና ወጥታ ብቻዋን ቀረች። ነፍስዋ በኀዘንና በብቸኝነት ድባብ ተዋጠች። ከአብርሃም አምላክ ከልዑል እግዚአብሔር በስተቀር ከላይም ከታችም አለኝ የምትለው አንዳች ወገን አልነበራትም። ስደትን ከቤተሰብ ወይም ከወገን ጋር መግፋት ይቻላል። ለብቻ ሲሆን ግን “በእንቅርት ላይ…”የሚሉት ዓይነት ይሆናል። ይሁን እንጂ ብዙ የእምነት አርበኞች በስደት ሀገር ገድልን በመፈጸም ለክብር በቅተዋል። ዋናው ነገር ከሀገር ርቆ መሰደዱ ሳይሆን ተሰድደው በሄዱበት ምድር ሁሉ “ተስፋሆሙ ለስዱዳን” የተባለውን መድኃኔዓለምን በልቡና ይዞ በጎ ፈቃዱን መፈጸም መቻል ነው።

አንዳንድ ሰዎች ከሀገራቸው በፈቃዳቸውም ያለ ፈቃዳቸውም ተሰድደው ሲሄዱ የራቁት ከተወለዱበትና ካደጉበት ቀዬ፣ ባህልና ኅብረተሰብ እንጂ ከእግዚአብሔር አለ መሆኑን ይረሱታል። ከአዲሱ አካባቢያቸው ጋር ለመላመድ ሲሉ ቀድሞ የነበራቸውን አመለካከት፣ እምነትና ሥርዓተ እምነት፣ መልካም ባህልና ወግ የማንነት መገለጫቸው የሆኑትን ዕሴቶች በሙሉ ከልቡናቸው አውጥተው ይጥሏቸዋል። በቀደመው ማንነታቸው ሁሉ ኀፍረትና ኋላ ቀር የመሆን ስሜት ይሰማቸዋል። ይኽ እውነታ በአብዛኛው የአፍሪካ ስደተኞች ይታያል ቢባል ማጋነን አይሆንም። (በአፍሪካ ግብፅ እያለሁ፤ በአውስትራሊያ አሁን ካለሁበት  ከማስተውለው  እውነታ አንፃር)

አፍሪካ የሰው ዘር ምንጭ፤ የሥልጣኔ መገኛ፣ የእምነት መሠረት ብትሆንም በተለያዩ ዘመናት በተለያዩ መልኮች ልጆቿን “ባርያ” ብለው ያፈለሱትና ቅኝ የገዟት “ኀያላን” ዜጎቿ ላይ ባደረሱት የሥነ ልቡና ተፅዕኖ አብዛኛው አፍሪካውያን የራሳቸውን ለመተውና የሌላውን ለማንሣት ይቀናቸዋል። ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ በመጣው ትውፊቷ፣ የራሷ ዜጎች በጻፏቸው መዛግብቶቿ፣ በተለያዩ ጥበበ ዕዷ፣ በረሃብ ከወየበው ገጿ ጀርባ ባለው ታሪኳ ለመታማመን የምዕራባውያንን “ማረጋገጫ” ማግኘት የግድ መስሎ ይታያቸዋል። ከአውሮጳውያን ተቀራማቾች ጋር ተያይዞ የተከሰተው በዘር በጎጥና በቋንቋ የመከፋፈልና የጦርነት ታሪካቸው የሚያሳፍራቸውን ያኽል ያንን አሳፋሪ ጠባሳ ለመቀየር ያላቸውን ዐቅም አሟጥተው “እስከ ጥግ” ለመትጋት አልቻሉም።

ኑኀሚን ከቤተ ልሄም ምድር ርቃ ምድረ ሞዓብ ወረደች። ቤተ ልሄም ግን በልቡናዋ ነበረች። የኤፍራታን ዜና አጥብቃ ትከታተል ነበር። ቤተ ልሄም በልቡናዋ ስለ ነበረችም አኗኗሯ ሁሉ ቤተ ልሄም እያለች ትኖረው እንደ ነበረውና እግዚአብሔርን በመፍራት እንዳጌጠው ኑሮ ነበር።

በኀዘንና በብቸኝነት ተከባ ሳለች ደስ የሚያሰኝ ዜና ሰማች። “እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደ ጎበኘ እንጀራም እንደ ሰጣቸው” ሰማች። ሩት 1፣6። ይኽ ለኑኀሚን ታላቅ ደስታዋ ነው። የእግዚአብሔር ሰዎች ለራሳቸው በሚደረግላቸው ነገር ከመደሰት ይልቅ ለሌላው እግዚአብሔር ያደረገውን ቸርነቱን በማየትና በመስማት ይደሰታሉ። ይኽም በሐዋርያው ቃል “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን አይመልከት፤ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ” ተብሎ ተነግሯል። ፊል.2፣3። እግዚአብሔር በረድኤት የሚገበኘው ሕዝብ ምስጉን ነው። እግዚአብሔር የረሃብና የኀዘን ዘመኑን አርቆለት በበረከት የሚገበኘው ወገን ምስጉን ነው። ቤተ ልሄም እንደ ስሟ ዳግም የእንጀራ ቤት ሆነች፤ ኤፍራታም ፍሬ ተገኘባት፤ ስም ከግብር ተስማማላት።

ኑኀሚን ሀገሯን አሰበች። መልክዐ ምድሩ ናፈቃት። አፈሩ ሸተታት። አየሩ ሽው አለባት። ከሀገሯ ረሃብ ገፍቶ አወጣት፤ ከሞዓብ ግን የሀገር ፍቅር ሰንሰለት ሊስባት ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ “ቁጣ እስኪያልፍ ድረስ ጥቂት ጊዜ ተሸሸግ” እንዳለው የረሃብ ዘመን እስኪያልፍ ድረስ ለእርሷ እንግዳ በሆኑ አሕዛብ መካከል ለመሸሸግ ተግድዳ ነበር። ኢሳ. 26፣20። የተሸሸገችበት ምድር ምንም እንኳን ዕንብርቷን ሊያቀላ፣ ሆዷን ሊሞላ የሚችል ምድር ቢሆንም ደስታን ሊሰጣት አልቻለም። ያን አካሏ የሆነ ባሏን፣ የማኅፀንዋ ፍሬ የሆኑ ልጆችዋን ያጣችበትን ምድር መከራው እስኪያልፍ ድረስ እንጀራ ብትበላበትም እስከ ወዲያኛው ሀገር ብላ ልትኖርበት አልወደደችም። ያ እትብቷ የተቀበረበት፣ አፈር ፈጭታ ውኃ ቀድታ ጮቤ ረግጣ ያደገችበት፣ ተኩላ ተድራ ወግ ማዕረግ ያየችበት ለአባቷ ለአብርሃምና ለዘሩ በቃል ኪዳን የተሰጠች ሀገር ናፈቃት። ስለሆነም “ከሞዓብ ልትመለስ ከሁለቱ ምራቶችዋ ጋር ተነሣች።” ሩት 1፣6። ግን በቤተ ልሄም ምን ነበራት? (ይቀጥላል)

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: